Tidarfelagi.com

ሃሳብ አትሞትም(ሶስት ታሪኮች)

በመካከለኛው ዘመን በመላው አውሮፓ መንግስት የነበረችው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ናት። ቤተክርስቲያን አምባገነን ነበረች። በሃይማኖት ስም ታስራለች ፣ ታሰቃያለች ፣ ትገድላለች። ሳይንስ ተቀባይነት ያለው ከሃይማኖቱ አስተምህሮ ጋር ስሙም ሲሆን ብቻ ነው። ከዚያ በተረፈ አዳዲስ ሃሳቦች ብቅ ካሉ መልሳ ትቀብራቸዋለች። ሶስት ታሪኮችን እንይ፦

፩) ኒኮላስ ኮፐርኒከስ ዳኒሻዊ የሂሳብ ሊቅ እና የክዋክብት አጥኚ ነበር። ከዚያ በፊት ምድር የአለም ማእከል እንደሆነች ተደርጎ ይቆጠር ነበር። ኮፐርኒከስ ግን ፀሀይን የሶላር ሲስተሙ ማእከል አድርጎ የሚያሳይ ሞዴል ነደፈ። ነገር ግን በዛ የጨለማ መካከለኛው ዘመን ይሄን መፃፍ ወይም መናገር እስከ ሞት የሚደርስ ከባድ ቅጣት ያስከትል ነበር። ስለዚህ ኮፐርኒከስ እስከ ሞቱ መቃረቢያ ድረስ ሳያሳትም አቆየው። ይሄንን አለም ከተሰናበተ በኋላ መፅሀፉ ታትሞ ብዙ አቧራ አስነሳ።

፪) ሌላው የሳይንስ ጠቢብ ጋሊልዮ ጋሌሊ ከጣልያን ምድር የኮፐርኒከስን ሂሊዮሴንትሪክ ሞዴል አስተጋባ። ኮፐርኒከስ ብዙም ስለማይታወቅ መፅሀፉ ችላ ተብሎ ነበር። አሁን ግን ጋሊልዮ በይፋ ሲያውጀው የቫቲካን ቁጣ ነደደ። ጋሊልዮ ከኢንክዊዝሺኑ ፊት ለፍርድ ቀረበ። የቀረበበት ክስ በመጽሐፉ ከቅዱስ መፅሀፍ ጋር የሚጣረስ ብዙ ነገሮችን በማስፈሩ ነው። በአጠቃላይ በኑፋቄ ወይም መናፍቅነት ተፈርዶበት የፃፈውን እንዲያስተባብል እና የቀረውን እድሜውን በቁም እስር አሳልፏል። ጋሊልዮ ፅሁፏን “ካስተካከለ” በኋላ ለቫቲካን በፃፈው ደብዳቤ እንዲህ ብሏል፦

“ምድር በፀሐይ ዙሪያ እንደማትዞር ልፅፍ እችላለሁ። ግን ይሄ እውነቱን አይቀይረውም። አሁንም ምድር በፀሐይ ዙሪያ መዞሯን ትቀጥላለች”

፫) ሶስተኛው ሳይንቲስት ጂዎርዳኖ ብሩኖ ነው። ጂዎርዳኖ ይህንኑ የኮፐርኒከስን ሞዴል በማስፋፋት “ፀሐይ ክዋክብት ነች። በህዋ ውስጥ ብዙ ክዋክብት አሉ። ሁሉም የየራሳቸው ፕላኔቶች አሏቸው። ዩኒቨርስ መጠን የለሽ በመሆኑ ማእከላዊ ነጥብ ሊኖረው አይችልም” በማለቱ ከሮማ ኢንክዊዚሽን ፊት ለፍርድ ቀረበ። በኑፋቄነት ተፈርዶበት በእሳት ተቃጥሎ እንዲሞት ተደረገ።

እነሆ ከብዙ አመታት በኋላ አሳቢዎቹ አልፈዋል፤ አሳዳጆቻቸውም ጭምር። የተደበቀው እውነት ግን ከዘመን ዘመን እየተገለጠ ፣ እየጎላ መጥቷል ። አሳቢዎችን እንጂ ሃሳቡን ማሰር፣ ማሰቃየት፣ መግደል አይቻላቸውም። ይሄም በዘመናት ተደጋግሞ የታየ እውነታ ነው። አሁንም ቢሆን ሃሳብን ለመግደል የሚሞክሩ በዙሪያችን አሉ። ግን አይሳካላቸውም። እንደውም አንድን እውነት ለማፈን በሚሞከርበት ወቅት ይበልጥ እየጎላ ነው የሚመጣው። እውነት ዘለአለማዊ እና ፍፁም ናት።

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...