Tidarfelagi.com

ሁለት ስፍራ፣ ሁለት ዓለም!

አስፋልት ዳር ያለች አነስተኛ ዳስ! ሃይለኛ ዝናብ ይዘንባል። ሰማዩ የላስቲክ ቤቷ ውስጥ ያለው መከራ ያነሳት ይመስል፣ ተጨማሪ መከራ ያዘንባል። ውስጥ… አንዲት እናት ተኝተው ያቃስታሉ።ምን ማድረግ እንዳለበት ግራ የገባው የአስራ ሁለት ዓመት ልጅ አጠገባቸውቁጭ ብሏል።የደረቀ እንባ አሻራውን ጉንጮቹ ላይ ትቷል። ሴትየዋ፣ ከጊዜያት በፊት፣ ፈጣሪያቸውን አመስግነው የሚኖሩባቸውን ቤት እያሰቡ፣ ህመማቸውን ያስታማሉ… ልጃቸውን እና ቤታቸውን የነጠቃቸውን ቀን…«እህ…እ…እ…» ያቃስታሉ።
«ቅድም፣ አንድ ሆቴል ሄጄ ትራፊ ምግብ ስለምናቸው ‘ሂድ ከዚህ’ ብለው አባረሩኝ። ትንሽ ምግብ እኮ ብታገኚ ይሻልሽ ነበር።»አላቸው ፊት ለፊታቸው ብርድ የሚያንቀጠቅጠው የልጅ ልጃቸው።
«አይይ፣ ልጄ ምኑም አላሰኘኝ።ይልቅ የሚያሳስበኝ ያንተ ነገር ነው»
ምግብ ከቀመሱ ድፍን ሁለት ቀናቸው።ምንነቱን ያላወቁት በሽታ ቀስፎ ያሰቃያቸዋል።ዝናቡ ሀይሉን ጨመረ።

ናዝሬት፣ በአንድ ትልቅ ሆቴል አዳራሽ ውስጥ!

በምግብ ዋስትና ራስን ስለማቻል ስልጠና ይሰጣል። ሰልጣኞቺ በትክክልም ራሳቸውን በምግብ የቻሉ ይመስላሉ።
መድረኩ ላይ አንድ ወጣት፣ ያዘጋጀውን የቁጥር መረጃ በፕሮጀክተር ለቤቱ እያሳየ፣ በጊዜያት ሀገሪቱን ራሷን በመመገብ መሻሻሏን ይሰብካል።በግብርናው ዘርፍ የተገኘው ውጤት አመርቂነት ይገልፃል። ሀገሪቱን ራሷን ከመመገብ አልፋ፣ የእህል ምርቶችን ኤክስፓርት ማድረግ ስለመጀመሯ ይደሰኩራል። ሰልጣኞቹ፣ አንዳንዷቹ ማስታወሻ እየያዙ፣ አንዳንዶቹ በገዛ ሃሳባቸው እንደተያዙ ያደምጡታል፤ያደመጡት ይመስላሉ።

የላስቲኳ ቤት፣

«አይዞህ ልጄ፣ እግዜር አለ፤ምንም አልሆንም»
ከሳምንታት በፊት፣ በሀና ማርያም የማያፈስ ቤት ነበራቸው።ለዓመታት የኖሩበት ቤት« ህገወጥ ነው» ተባለ።
ልጃቸው፣ «ተያቸው የሚያደርጉትን እናያለን»አለ። በትርምሱ ሰዐት ከሞቱት መሃል ልጃቸው አንዱ ሆነ።የሚያደርጉትን አየ። የአስራ ሁለት ዓመት ልጁን ያለ ቤት ጥሎባቸው ሞተ።
ዝናቡ በሀይል ይረግጠዋል! በመከራ ላይ ተግቶ መከራ ይደርባል።የልጅ ጥርሶች ይንቀጫቀጫሉ።
«መንግስትስ እሺ… የሰማዩ ምን በደላችሁኝ ብሎ ነው»አሉ እላያቸው ላይ ያለውን አዳፋ ብርድ ወደ ሰውነታቸው እየሰበሰቡ።የልጅ ልጃቸው በብርድ እና በጭንቀት ተኮራምቶ ያያቸዋል።ሰውነታቸው እየደከመባቸው ሄዷል።
«የኔ ልጅ፣ ጥሩ ልጅ ሁን እሺ» የድምፃቸው ጥንካሬ ሸሽቷል። በደከመ ድምፅ ያቃስታሉ።
«እሺ አያቴ… ትድኛለሽ እሺ አያቴ»
«ጥሩ ልጅ ሁን…»
«አይዞሽ አያቴ እግዜኢአብሔር ያድንሻል»
በረጅም አቃሰቱ።
«አያቴ?!! »
ዝም! ደገመ። አሁንም ዝም። በፍርሃት እጆቹን ልኮ ነቅነቅ አደረጋቸው። ምንም! ድምፁን ከፍ አደርግ አንጀት የሚበላ ለቅሶ ያለቅስ ጀመር። ለቅሶው በዝናቡ ውስጥ ተዋጠ።

ስልጠናው ወደ ማለቂው ደርሷል። አስልጣኙ የማጠቃለያ ንግግሩን አሰማ።
«የዛሬ ስልጠናችንን በዚህ ጨርሰናል። ባለፉት ተከታታይ ሶስት ቀናት ጥሩ ጊዜ እንዳሳለፍን ተስፋ አደርጋለሁ። የስልጠናችን ቆንጆ መዝጊያ እንዲሆንም፣ የእራት ግብዣ አዘጋጅተናል። መልካም እራት ይሁንላቸሁ።» ደማቅ ጭብጨባ!
ሰልጣኞቹ እራት ወደ ተዘጋጀበት ስፍራ፣እርስ በርስ እየተገፋፉ መውጣት ጀመሩ። መገፋፋታቸውን ላየ፣ የመጨረሻ እራታቸው ይመስላል።

የራስ ናቸው፡፡ የማንንም ሃሳብ ለመፃፍ አልተከፈተም! የሚያስማሙንን ሃሳቦች እዚህ ካገኛችሁ እሰየው፡፡ ለመስማማት አንፅፍም፣ ለመፃፍ አንስማማም፡፡ ወዘተ

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...