Tidarfelagi.com

ሁለቱን ባሎቼን ላስማማ እያሸማገልኳቸው ነው (ክፍል ስምንት)

‘ጊቢ ግቡ’ እስኪባል ድረስ ምን መወሰን እንዳለብኝ ግራ ገባኝ። ማንም FBE በLAW እንደማይቀይረኝ እያወቅኩ ሞከርኩ። ላለመማርም አስቤያለሁ። ከዛ ልጄን ይዤ የሆነ ቦታ እልም ብዬ መጥፋት ……. ማንም የማያውቀኝ ቦታ ሄጄ ከዜሮ መጀመር። በእኔ እልህ ልጄን ማስከፈል የማይታሰብ ነው። እጅ መስጠትም ምርጫዬ አልሆነም። ልክ ጊቢ ግቡ ሲባል አሁንም አቧራዬን አራግፌ ተነሳሁ ……. እማራለሁ …….. ጥሩ ውጤት አመጣለሁ ….. ለሚጠብቀኝ ሁሉ ኩራት እሆናለሁ …… ከማንም በላይ ራሴን እና ልጄን አኮራለሁ …….. ቀና ብላ የምትሄድ ሴት እሆናለሁ ……. ህይወቴን ሳሸንፍ የሆነ ቀን ህግ እማራለሁ። ራሴን ሳፅናና “ያውም ህግ መማር የምፈልገው ወንጀል ነክ መፅሃፎች ለመፃፍኣ? እደርስበታለሁ”
እሱን? ግራ ቂጡን ትወጋዋለች ብላችሁ ነው የምትጠብቁትኣ? አልገባችሁም ግራ ቂጤ እስኪጨስ እንደማፈቅረው።
“አምላክ ሆይ እባክህ ለሱ ያለኝን ፍቅር ውሰድልኝ አልችልም ብዙ ነው” ብዬ የምፀልይ ሰገጥ እንደሆንኩ አልገባችሁም። በዚህ ሁሉ ውስጥ እንዴት እንደምወደው ቢያውቅልኝና ድሮ እንደማውቀው ‘እሱ’ ፍቅራችንን ብንኖረው ስለቴ እንደሆነ አልገባችሁም። በዚህ ሁሉ ውስጥ ለነገ አብሮ ኑሮኣችን መሰረት ይሆነናል ብዬ ከወር ደሞዙ ላይ የሚከፈል መሬት በሊዝ እንደዳስገዛሁት አታውቁማ (ለዛዛ በሉኝ ስትፈልጉ።)
እናም ተውኩለት “ይቅር ብዬሃለሁ” አልኩት “ካንተ አይበልጥብኝም!” አልኩት በአዋቂ ደንብ ቁጭ ብለን አወራን (እኔ 20 ዓመቴ እሱ 25 ነበርን ይሄ ሲሆን ለሚያጠፋቸው ጥፋቶች ለራሴ ከምሰጠው ምክንያት አንዱ ‘ስላልበሰለ ነው ወደፊት እንዲህ አይሆንም’ የምለው ነገርስ? የሆነች አሮጊት ሴትዬማ ውስጤ ነበረች )
“ይሄን ማሪኝና ሁን ያልሽኝን ልሁን” አለኝ። ከዛም እሱም የማታ ኢኮኖሚክስ MA ሊማር ተመዘገበ።
ጊቢ የገባሁ ቀን አብሮኝ ሄደ። ከዘበኛው የጀመረ በጋሞኛ ሰላምታ እየሰጠ ሚስቱ መሆኔን አበክሮ እየነገረ። ፕሮክተር ነሽ ወጥ ቤት ያልዞረበት የለውም እጄን ይዞ ……. እንዴት እንደሚያወራ ያውቅበታል። ስቆ አያውቅም የሚባል ሰፊ ፊት ማስፈታት ያውቅበታል።
“ባልሽ ግን ‘የሜሪ ባል ነኝ’ እያለ ራሱን የሚያስተዋውቀው ማነሽ ብሎ ነው የሚያምነው ሴሌብሪቲ ነው እንዴ የምትመስዪው?” ብሎኛል አንዱ የአርክ ተማሪ ‘ሚስቴ ናት’ ሲል ኩራቱን አይቶት …..
አብረን ዶርም ድረስ ሄድን:: አልጋዬን አንጥፎልኝ። ዶርሚተሪዎቼን ተዋውቆ ሲያስቀን ቆይቶ ወደቤት ተመለሰ።
“ወንድምሽ ነው?” ሲሉኝ የምበሳጨው መበሳጨት
“ባሌ ነው። የልጄ አባት እሺ” እላለሁ:: በነገታው አዳዲስ ልብሶች ገዝቶልኝ መጣ። ግራ ገባኝ ምክንያቱም ብር እንደሌለው አውቃለሁ። ከሁለት ቀን በኋላ እቤት ስሄድ ቴሌብዥኑን እንደሸጠው አየሁ። እኔ እንደሱ ‘አልበላ አልጠጣ ብዬ የገዛሁትን …… እንዴት አትነግረኝም’ አላልኩም:: ዶርም የገባሁ ቀን ቱታ እንደለበስኩ ነው የሄድኩት ሴቶቹ ዘንጠው ሲያያቸው ሚስቴ ከነሱ አትነስብኝ ብሎ እንዳደረገው ገብቶኛል አቅፌው አለቀስኩ ብዙ እንደምወደው ነገርኩት…..
እኔ የሀብታም ልጅ አይደለሁም። ግን ቤተሰቦቼ ባላቸው አቅብጠውኝ ነው ያደግኩት። እሱን እስካገባሁበት ሰዓት ድረስ እግሬን ሰራተኛ ያጥበኝ ነበር። ሀብታሞች የሚማሩበት የግል ትምህርት ቤት ነው የተማርኩት። ይሄ ሁሉ ሆኖ ካነበብኳቸውም መፅሃፍት ሆነ መፅሃፍ ቅዱስ ከሚታየው የላይ ለውጥ ራሴን ውስጤን ስለመቀየር እንድጨነቅ ነው አብዝቼ የተማርኩት። ልብስና እህል በፍፁም ብርቄ አይደሉም። ስለእውነቱ ከእኩዮቼ በተሻለ የምፈልገውን በእድሜዬ አጊጫለሁ። እዛ እድሜዬ ላይ ቁሳቁስ የሚያሳስበኝ ሴት አልነበርኩም። ሀብት ካፈራሁ የምመኘው ከእርሱ ጋር ስለምናፈራው ሀብትና እኔና እሱ ከልጆቻችን ጋር ስለምንኖረው ድሎት እንጂ ጊቢ እገሊት የለበሰችው ቀሚስ ግድ የሚሰጠኝ ሴት አልነበርኩም። ለእሱ ግን ለእኔ የሚያስፈልገኝን አለማሟላት ሞቱ ነበር። የቤተሰቤ ቤት የሚናፍቀኝ …… የማያቸው ሰዎች የሚያስቀኑኝ ይመስለው ነበር ……. ላስረዳው ይቸግረኛል።
ተማሪዎቹ ስልክ ስለነበራቸው የሱን ስልክ ለእኔ ሰጠኝ። ‘ስትናፍቂኝ እኔ መጥቼ አይሻለሁ ስልክ እኔ ምንም አያደርግልኝም’ አለኝ ስለእውነቱ ለእኔ ከሚያደርግልኝ በላይ ለእርሱ ያደርግለት ነበር።
አንደኛ ሴሚስተር አርባምንጭ ተማሪ በማባረር አንደኛ ነው ብለው አስፈራርተውኝ ስለነበር ድምፄን አጥፍቼ ትምህርት ላይ አደፈጥኩ። ያው በሳምንት ብዙውን ቀን ነው እሱጋ የማድረው ዶርም ያደርኩ ቀን ደግሞ ስለእርሱ እያወራሁ ሳደነቁራቸው አድራለሁ። እሱም በሳምንት ብዙውን ቀን ትምህርት ቤት ጊቢ ይመጣል። ማታ ከክላስ መልስ ጊቢ ውስጥ አቅፎኝ ሲንጎራደድ ትምህርት ቤቱን የገዛ ባለሃብት ነው የሚመስለው። የሚያየን ሁላ ታድለሽ ባልሽ ደስ ሲል እንዲህ ዓይነት ባል ቢኖረኝ’ የማይቀናብኝ የለም።
ነፃነቴን በሆነ መልኩ እንደያዘው ባውቅም አልጎረበጠኝም። ለምሳሌ ከጠዋት እስከማታ የለበስኩትን ያገሳሁትን የበላሁትን የሄድኩበትን የፈሳሁትን ፈስ ቁጥር ልክ የሚነግሩት ሰዎች አሉት። አውቃለሁ። ከእሱ ተደብቄ የማደርገው ነገር ስላልነበረ ግድ የለኝም። ቢበዛ ‘ዛሬ ለብሰሽ የነበረው ቦዲ ግን አልሳሳም? ደረብ አታደርጊም?’ ቢለኝ ነው። ወይም ከጓደኞቼጋ ሻይ ልንጠጣ ወደከተማ ስንወጣ ከየት መጣ ሳንለው ዱብ ብሎ ሰላም ብሎን ይሄዳል። ወይም ስንጨርስ ‘ባልሽ ሂሳብ ከፍሎላችሁ ነው የሄደው’ እንባላለን ሳናየው
“ይሄ መንፈስ የሆነ ባልሽ ትከሻዬ ላይ ዱብ እንዳይል” ይሉኛል ጓደኞቼ ሙድ ሲይዙ የሆነ ቦታ ስንሄድ
ደስተኛ ሆንኩ። ደሞኮ ብዙ የማልፈጀው ነገሬ ….. በቃ ደስተኛ አደረገኝ …… የመጀመሪያ ሴሚስተር ውጤት መጣ። ሁሉንም ትምህርት A ሳመጣ ካልኩለስ B አመጣሁ። ካልኩለስ አስተማሪያችን ሴት ናት (ይሄን ፅሁፍ አታየውም ብዬ ተስፋ ላድርግ) ቂጧ ትልቅ የሚያምር …… ስታስተምረን ፊቷን አዙራ አዳሜ ይቸክልና ልክ ስትዞር ሁሉም በልቡ ኤጭ የሚል አይነት ይመስለኛል። ያልሰራሁት ጥያቄ በጣም ቀላሉን ስለነበር በዛ ላይ ሴት መሆኔ በዛ ላይ ሌሎቹን በሙሉ A ማምጣቴ ይመስለኛል ቢሮ አስጠራችኝ።
“ከባዱን ሰርተሽ ቀላሉን ነው የሳትሽው” አለችኝ
“ካልኩለስ የመጨረሻ ቀን አልነበር? የልጄ ልደት ነበር ፈተናውን ቶሎ ሰርቼ ሀዋሳ መሳፈር ነበረብኝ ስቸኩል መሰለኝ የሳትኩት!” አልኳት
“ልጅ አለሽ?” አለችኝ
“አዎ ሁለት ዓመት ሆናት። ቤተሰቦቼጋ ነው ያለችው እኔና ባሌ እዚህ ነው የምንኖረው ብዬ ” ያልተጠየቅኩትን መቀባጠር። ዝም ብልስ ኖሮ?
ደስ ብሏት ስታደንቀኝ ቆየችና ምንም ብፈልግ እንደምታግዘኝ ከጎኔ እንደሆነች እንደምታግዘኝ ምናምን ነገረችኝና
“ባልሽ እዚህ ከተማ ነዋሪ ነው?” አለችኝ ባትጠይቀኝስ እሷስ ቢቀርባት? እኔ ደግሞ ስለእሱ እንኳን ተጠይቄ ሳይጠይቁኝ የፍቅር እስከመቃብርን ትረካ ያህል ክፍሎች ያለመታከት እተርካለሁ።
“አዎ እገሌ ይባላል! እንዴ ታውቂዋለሽኮ የማታ ታስተምሪዋለሽኮ ስላንቺ እንደውም አውርቶልኛል …. ረዥም እንኳን …. ጠይም ቆንጆ ዓይኖቹ ትልልቅ ……” እኔ እለፈልፋለሁ እሷ ስሙን ከሰማች በኋላ ደንዝዛለች። በልፍለፋዬ መሃል አስተዋልኳት አሳዘንኳት ወይም ለራሷ አዘነች ወይም አላውቅም እጄን ጥብቅ አድርጋ ይዛኝ
“አንቺ ብርቱ ሴት ነሽ ምንም ነገር እንዳይበግርሽ እሺ? ልብሽን ጠብቂው በናትሽ። አደራ በርቺ” አለችኝ። እንስ ስል ታወቀኝ….. በቃ ቅንስ …… ኩምሽሽ ።
ስለሷ ያወራነውን ሁሉ ገጣጠምኩት። ብትን ብዬ የምፈነዳ ነገር መሰለኝ። ከምሽቱ 4 ሰዓት ወደከተማ የሚሄደውን የመጨረሻ ታክሲ ይዤ እቤት ደረስኩ። በሩን በርግጄ እንደገባሁ ፈነዳሁ።
“አንተ በእኔ ላይ? ያውም ከአስተማሪዬ ጋር (ያውም ከዛ ቂጥ ጋር ብለው ደስታዬ ነበር?) ወይኔ ሜሪ !!
አበድኩ ሊሰደቡ የሚችሉ ስድቦችን ሁላ ብልግና ስድቦች ሳይቀር ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳደብኩ። ብቻዬን እየተቀነጣጠስኩ ስውረገረግ ለመጀመሪያ ጊዜ ዝምምምምምም አለ።

3 Comments

 • ሐረገወይን ተስፋዬ commented on July 14, 2021 Reply

  ውይ ሜሪዬ አለቀ ባላልሽኝ ቀጣዩን በጉጉት እጠብቃሁ

 • Jemytexas@gmail.com'
  የጁጁ አባት commented on July 15, 2021 Reply

  እንቅልፍ አልወስድም አሉኝ። ቀጥይልኝ በናትሽ።
  ተፃፈ ከ ሌሊቱ 10:41

 • yeabkonjonat@gmail.com'
  Yeabyeyilma commented on July 16, 2021 Reply

  Ere ketayun part plz

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...