Tidarfelagi.com

ሁለቱን ባሎቼን ላስማማ እያሸማገልኳቸው ነው!! (ክፍል አራት)

 በሚንቀጠቀጡ እጆቼ ደመነፍሴን ቢላ አንገቴ ላይ ያደረገ እጁን ለቀም አድርጌ ያዝኩት። ያዝኩት እንጂ እንዲያሸሽልኝ ልገፋው ወይ ራሴን ላሸሽ አቅሙ አልነበረኝም። የአቅሜ ጥግ ሳጌ ድምፁ እንዳይሰማ አፍኜ እንባዬን ማዝነብ ብቻ ነበር። እጁ አንገቴ ላይ ቢላዋ መደገኑን እጆቼ ሲይዙት ገና ያወቀ ይመስል ደነገጠ። በጣም ቀስ ብሎ እጁን አወረደው …….. ቢላውን ወረወረው …….. በጣም ቀስ ብሎ መሬቱ ላይ ተቀመጠ። አንገቱን ወደመሬቱ ደፍቶ እንባው መሬቱ ላይ ተንጠባጠበ። ይሄኔ ‘ዋጥ አድርጋት’ ተብሎ ታፍኖ እንደተገረፈ ህፃን “ህእእ ህእእእ ……” ብዬ ድምፄን አውጥቼ ማልቀስ ጀመርኩ።
ይሄኛው ሌላ ሰውዬ ነው። የእኔ ባል እንኳን ቢላዋ አንስቶ አንገቴ ላይ ሊያደርግ እጅሽን ይቆርጥሻል ብሎ ሽንኩርት የሚከትፍልኝ …… ትልልቅ አይኖቹ እያለቀሱ ሲያስቸግሩት
“እማ ቆይ ወጥ ያለሽንኩርት ቢሰራ ምን ይሆናል?” የሚለኝ
“እሺ አንተ ነጭ ሽንኩርቱን ላጥልኝ ሽንኩርቱን እኔ ልጠዋለሁ” ስለው ሊልጥ ይታገልና
“እማ ቆይ ወጥ ውስጥ ነጭሽንኩርት ባይገባ ምን ይሆናል?” የሚለኝ።
“እህ? እና ያለሽንኩርት ያለነጭሽንኩርት ዘይት ላይ በርበሬ አድርገን እናቁላላ? “
“አንቺ ከምትቃጠዪብኝ አይሻልም?” እያለ የሚያባብለኝ። ሁሉ ነገር ከእሱ ሲወዳደር የሚያንስብኝ የኔ ባል ይሄ ነው።
የኔ ባል በቀደም በእግር እየሄድን ከእርግዝናው ጋር ተያይዞ በመጣ ደም ማነስ አዙሮኝ ስወድቅ እንደህጻን በእጆቹ አቅፎ ሀኪም ቤት ያደረሰኝ።
“አባ መራመድ እችላለሁ እኮ!” ስለው
“እኔ ምን እሰራለሁ?” የሚለኝ ዶክተሩን
“ደም ማነስ እንዴት አዙሮ ይጥላታል? ደግመህ መርምርልኝ ካለበለዚያ የሆነ ነገር ብትሆንብኝ እጣላሃለሁ!” ብሎ የሚቀውጠው
“ፈሳሽ ነገር በብዛት መውሰድ አለባት!” ብሎ ሲለው። ያለ የሌለ የጁስ መዓት እያስጠጣኝ በሽንት ብዙት የረጋ እንቅልፍ የማያስተኛኝ
ለእኔ ከሆነ ምንም የሚያደርግ የትም የሚሄድልኝ።
የኔ ባል ገና ለከተማው አዲስ ሆነን እንደመጣን አንዱ ቸርች ይዞኝ ሄዶ “ባለቤቴ ናት የሚያምር ድምፅ አላት እኔም እሷም ጌታን ማገልገል እንፈልጋለን ብሎ ኮስተር ብሎ ሲያወራ (ማስፈራቱ ግርማሞገሱ ደግሞ ) ከሳምንታት በኋላ አብሬው ማስመለክ የጀመርኩት ……
ከእግዜር ጋር ያለኝን ፀብ በሚገባኝ ጣፋጭ ቃል አይኔን ከሰዎች ላይ እና ካልተደረገልኝ ነገር ላይ አንስቼ ትልቁ አምላክ ላይ እንዳደርግ ያስተማረኝ መምህሬ …….
እንኳን እኔ ወንድሜ እጁን ይዞ ፒያኖ ያስተማረው። ወንድሜ ምን መሆን ትፈልጋለህ ቢባል “እሱን” የሚልለት የሚያስቀና ስብእና ያለው (ያሸነፈኝ ምን ሆነና?)
የኔ ባል
ጎረቤት ዶሮ ወጥ ተሰርቶ አይቼ ከስራ ሲመጣ እያለቀስኩ “ወጥ ሰርተው እንብላ እንኳን ሳይሉኝ ወደቤት አስገቡት!” ብዬ ስነግረው በአንድ እርምጃ የሰው ቤት ገብቶ
“እንዴት ሚስቴ እርጉዝ መሆኗን እያወቃችሁ ወጣችሁን ከለከላችኋት?” ብሎ የሚጣላልኝ። በሰው ዶሮ ወጥ ‘እሷ የምትወደው እግር ነው’ ብሎ መርጦ ይዞልኝ የሚመጣ …
የኔ ባል “መንገድ ላይ ጮክ ብሎ መዘመር አማረኝ” ስለው እንዘምራለና ታዲያ ብሎ በሰው ሀገር መንገድ ላይ ቀውጢ አምልኮ ፈጥረን ሰው ከመንገዱ የምናሰናክል …..
“አባ ደከመኝ ትንሽ እንረፍ!” ስለው እሽኮኮ ካላደረግኩሽ ብሎ የሚያስቸግር …
መንገድ እየሄድን በሃሳብ ተውጬ የሆነኛው መንገድ ላይ የተንጠለጠለ ሙዝ ላይ ሳፈጥ የሰው ማሳ ገብቶ ያልበሰለ ሙዝ ሰብሮ ከጠባቂው ጋር ግብ ግብ የሚገጥምልኝ ….
የኔ ባል ሁለት ልጆች አንድ ሴትና አንድ ወንድ ወልደን ስማቸውን አውጥተን ስናረጅ ምን እንደምንሰራ አቅደን። ፀጉራችን ነጭ ሆኖ ጥርሳችን አልቆ ምን እየተባባልን እንደምንፎጋገር አውርተን የጨረስን ….
የኔ ባል “ባንተ ድምፅ ሲሆንኮ ሲጣፍጠኝ” ስለው ቁጭ ብሎ መፅሃፍቶች የሚያነብልኝ።
ሰው ውጪ ምሳ ልጋብዝህ ሲለው ሚስቴ ብቻዋን ናት ብሎ የሚመጣልኝ …
የእኔ ባል ብዙ ነው …… በእያንዳንዱ በሚያደርጋቸው ጥቃቅን ነገር ሁላ ሳይቀር ከምንም እንዳላወዳድረው ሆኖ ልቤን የሞላ ነው
…..
ይሄኛው የኔ ባል አይደለም። እንዴት ሁለት ማንነት አንድ ስጋ ውስጥ ይቀመጣል???
…..
…..
ለሰዓት ያህል ከተቀመጥንበት እሱ ቀድሞ ተነሳ
“ሄጄ አምሳሉን (ስራ በመስራት የምታግዘን ልጅ ናት) ልጥራትና እሷ ወጡን ትስራው በቃ ወይም ይቅር በቃ ስጋ ገዝተን ጠብሰን እንብላ …..አይሻልም ? ….. አንቺ ተነሺ በቃ አረፍ በይ እ?” ሊወጣ መንገድ ከጀመረ በኋላ
“የትም አትሄጂብኝምኣ?” አለኝ እግሬ ስር መጥቶ ጉልበቴን እያሻሸ
“ልሂድ ብል የት እሄዳለሁ?” አልኩት ሳላስበው። በዛ ቁመቱ ዝርፍጥ ብሎ ስሬ ቁጭ አለ። በእርግዝናው ሳቢያ ማበጥ የጀመሩ እግሮቼን ከጫማው ላይ አንስቶ ሁሌን እንደሚያደርገው እያሸልኝ
“እማ እባክሽ ማሪኝ!” አለኝ እንባው ጠብ ሲል እግሬ ላይ ያርፋል። እሺም ..እንቢም … ሙግትም … ትግልም … የለኝም ብቻ ፀጥ !!
“እማ እባክሽ አትተይኝ! ???ይቅር በይኝ!??” ከማልቀስ ውጪ መልስ አልሰጠውም። ሁሉም ነገር ግልብጥብጥ ብሎብኛል የተፈጠረው ቅፅበት ህልም ቢሆን ….. እሱን ክፍል ብቻ መደምሰስ ብችል ከጭንቅላቴ ውስጥ ….. ለምን? እንዴት? ጭንቅላቴ ውስጥኮ ብዙ ጥያቄ ይንከላወሳል።
እንዴት አንድ የዚህኛውን እሱን ምልክት ይሄን ያህል ጊዜ አላየሁበትም? ግን አፌን ለቆ የሚወጣ ምንም ቃል የለም። ልጅ ልኮ የምትሰራልንን ሴት አስጠርቷት አመት በአል አስመስላው ሄደች እንደነገሩ እራታችንን ቀማመሰን በጊዜ ተኛን። እኔና እሱ ኩባያ የምንለውን አስተኛነት (ለምን እንደዛ እንዳልነው አላስታውስም) ጀርባዬን ሰጥቼው በጎኔ በእጆቹ በሃል ታቅፌ ጀርባዬና ደረቱ ተጣብቀው …. እጥፍ ያለ ጉልበቱ መሃል እግሮቼን አጥፌ ተኛኝ። ማልቀሴን ማቆም አቃተኝ። ሳጌ እንዳያመልጠኝ እታገላለሁ።
እያለቀሰ ነው። ሳጉን እንዳልሰማው ውጦታል። እንባዬ ክንዱን ሲያርሰው ይሞቀዋል። እንባው አንገቴ ስር ሲያርሰኝ ይሞቀኛል። አልቅሼ እንባዬ ሲያልቅ ነው መሰለኝ …
“ምን ያህል እንደማፈቅርህ ህቅ ህቅ (ሳጌ ያቋርጠኛል) አልገባህም ማለት ነው?” አልኩት ዞሬ
“እማ እባክሽ ማሪኝ?” አንገቴን ፀጉሬን እጄን በእንባ የራሱ ጉንጮቼን አይኖቼን ይስማቸዋል። ለደቂቃዎች ምላሳችን ላይ እንባችን ጨው ጨው እያለን ስንሳሳም ቆይተን ደረቱ ላይ እንቅልፍ ይዞኝ ሄደ።
በነገታው ለሱ ሳልነግረው ከቤት ወጥቼ እናቴጋ እቤት ስልክ ደወልኩ። የተፈጠረው ነገር ለሱ ያለኝን ፍቅር አልነበረም የቀነሰው። እኔኑ ራሴኑ ነበር በሆነ መጠን የሸረፈኝ። ምክንያቱም ከትናንት በፊት የነበረችው ሜሪ ለማንም ብላ ማንንም የምትፈራ ሴት አልነበረችም።
በስልኩ ውስጥ የእናቴን ድምፅ ስሰማ። ማውራት አቃተኝ!!! እንባ እና ህቅታ ብቻ ….

One Comment

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...