Tidarfelagi.com

ሁለቱን ባሎቼን ላስማማ እያሸማገልኳቸው ነው!! (ክፍል አምስት)

“ማሚ” ከማለቴ እናቴ በስልኩ እልልታዋን አቀለጠችው። ፀሎት አይሉት ወሬ
“ጌታ ሆይ ምን ይሳንሃል? ጸሎቴን ሰማኸኝ እልልልልል …… ልጄ? ደህና ነሽ?”
“ደህና ነኝ!” እያልኳት እሪታዬን እለቀዋለሁ
“ምን ሆነሽ ነው? የት ነው ያለሽው ?አሁኑኑ ልምጣ ?”
“ምንም አልሆንኩም! ናፍቃችሁኝ ነው።”
ስለእሱ ላወራት አልችልም። እሱን ከማሳማው ያን ቢላ አንገቴ ላይ ድጋሚ ባገኘው ይቀለኛል። እሱን እንድትጠላብኝ አልፈልግማ!! ልጇን ያደረጋትን እንጂ ልጇ ለሱ ያላት ገደብ የለሽ ፍቅር አይገባትማ! ግን የእናት ሆዷ ነግሯታል።
“እሺ ይሁን እንዴት ሆንሽ? ትምህርትሽን እየተማርሽ ነው? “
“አይደለም ማም እርጉዝ ነኝ። በዚህ ዓመት አልማርም። ልጄን ከወለድኩ በኋላ እማራለሁ!”
ዝም አለች። ወደፊቴን አስባው ልቧ ዝሎባት መሰለኝ ዝም አለች። ከወለዱ ኋላ ያለውን አቀበት አይታው ነው መሰለኝ ዝም አለችልኝ። የምትለው የማታጣው እናቴ ዝም
“ማም ?”
“ወዬ? እስኪ ይሁን ብቻ አንቺ ደህና ሁኚ!….. እሱ አሁን አጠገብሽ አለ? (አባባሏ ይሄ እንትን …. ብላ የሆነ ስድብ የመቀጠል ነገር ነው። )ምንም ባልላትም ጠምዳዋለች።
“የለም ስራ ነው!”
“ይሁን እንደምትዪው ….. በወጉ ሽማግሌ ላክ በዪው ….. ሳትወልጂ በስነስርዓቱ ተደግሶ ቃልኪዳን ትፈፅማላችሁ። በምንም ሁኔታ ቢሆን ልጄን እንደማልተውሽ ማወቅ አለበት።”
“ማሚ እሱኮ ከእናንተ እንድጣላ አይፈልግም ለምን እንደጠላት ታዪዋለሽ? ምርጫዬን የመረጥኩት እኔ ነኝ እሱ እንደውም ሁሌ ደውዪላቸው ነው የሚለው።” (ደግሞ የምሬን ነው። በከፋኝ ቁጥር ለምን አትደውይላትም ነበር የሚለው)
“እሱን እንኳን ተይው …. የውልሽ ልጄ ወንድ ልጅ ብቻሽን ሲያገኝሽ እና መሄጃ እንደሌለሽ ሲያውቅ ጥሩ አይደለም። ያኔ ከርሱ ውጪ ምርጫ የሌለሽ ንብረቱ ነሽ። ያን ክፍተት አትስጪው …… አይደላደል ….. ተንከባክቦ በፍቅር ካላኖረሽ አማራጭ ያለሽ መሆንሽን ሲያውቅ እንደሚገባሽ ያከብርሻል!!”
የኔ ባል ይለያል ብዬ እንዴትም ላስረዳት አልችልም። እናቴ አንድም በህይወቷ ሴትነትን ከፍ አድርጋ የምትኖር ሁለትም ሴቶች ጉዳይ የምትሰራ ያውም በከፍተኛ ሃላፊነት ደረጃ ላይ ያለች ሴት ናት።
“What happen to ስታስተምሩ ያሳደጋችሁኝ ‘ሚስት ለባሏ ትገዛ?'”
“ሚስት ለባሏ ትገዛ ሲል ለባልም ሚስቱን ነፍስን እስከመስጠት ባለ የክርስቶስ ፍቅር የመውደድን ሀላፊነት እንደሰጠው አትርሺ!” አለችኝ ኮምጠጥ ብላ።
“ማሚዬ እንደዛ ይወደኛል።” አልኳት ለእሷ … ለራሴ መልሼ ግን ‘እንደዛ ይወደኛል?’ ብዬ አሰብኩ። ያልጠየቀችኝ ነገር የለም።
“ለመሆኑ ቤቱን በትክክል ያስተዳድራል?” ምን ማለቷ እንደሆነ አውቃለሁ። ገንዘብ ይሰጥሻል ወይ ነው?
“ማሚ ደሞዙን አምጥቶ ለእኔ ነው የሚሰጠኝ (የምሬን ነው። ሙሉውን ደሞዝ አምጥቶ ለእኔ ነበር የሚሰጠኝ። ልክ አባቴ ለእናቴ እንደሚያደርገው። በወር የሚያስፈልገንን ፅፌ አዘጋጃለሁ። ለሱ የኪስ ብር እሰጠዋለሁ። የሚደረገውን ሁሉ እኔ ነኝ የማደርገው። )
“እሺ ጉዳዩ ላይ እንዴት ነው?”
“ማሚ ኸረ በጌታ ?” ለቅሶዬን አስትታ አስፈገገችኝ
“እህህ የምሬን ነው። ከዚህ ሰው ጋርኮ ነው የምታረጂው። ትዳር እኮ ቆይ ለጉዳዩ ለጉዳዩ ጊዜ ወጣ ብዬ ልምጣ አይባልበትም!”
መጨረሻ ላይ አባቴን ላወራው እንደምፈልግ ስነግራት። እሷ ሰበብ ብትነግረኝም አባቴ ሊያናግረኝ እንዳልፈለገ ገባኝ። ዝምተኛው አባቴ በዝምታው ሊቀጣኝ ፈልጓል። ሁሌም እንደዛ ነው። ጥፋት ሳጠፋ ተቆጥቶኝ አያውቅም። በዝምታ ነው የሚቀጣኝ። ጥፋቴን እስካርም ወይም ይቅርታ እስክጠይቅ ድረስ አያዋራኝም። ይሄኛውን ግን ለማረም ዓመታት ሊፈጅብኝ ይችላል። እሱ የሚስላትን ልጁን ሆኜ ላሳየው ብዙ ይፈጃል እና በዝምታው የሚቀጣኝ እስከዛ ከሆነ?……
የዛን ቀን ማታ ከስራ መጥቶ ወክ እያደረግን ለእናቴ እንደደወልኩ ልነግረው ፈራሁት። ምኑ እንዳስፈራኝ አላውቅም። ካፈቀርኩት ጀምሮ ከሱ ጋር ሳልማከር አድርጌ የማውቀው ነገር ባለመኖሩ ስለደበቅኩት? ‘ግን እናቴጋ ለመደወል የግድ ከእርሱ ጋር መማከር አለብኝ?’ እላለሁ ለራሴ ነገሩን ለማቅለል።
“አባ ዛሬ ማሚጋ ደወልኩኮ!” መገረምም መደንገጥም ፊቱ ላይ እያየሁ ምንም እንዳልመሰለው ለመሆን ጣረ ሁለታችንም እየተቀየርን እንደሆነ አሰብኩና ፈራሁ። መደባበቅ እየጀመርን ነው። ፈራሁ!!
“ቆንጆ አደረግሽ! ምን ተሰማሽ? ደስ አለሽ? ማሚ ምን አለች? ደህና ናቸው?” ስሜቱን ለመደበቅ በጥያቄ ያጣድፈኛል። ያለችኝን ነገርኩት
“ደስ ይላል እማ!” አለኝ ማንን ሽማግሌ እንደሚልክ ምናምን ሰርጋችን ላይ ማን እንደሚጠራ ምናምን ማውራት ጀመርን!!
ስለሰርጋችን ማውራቴ ትቼው ልሄድ አለማሰቤን ስለነገረው ይመስለኛል ቀለል አለው። እኔ ግን ከፋኝ !! እኔ እና እሱ መሰለኝ እየተባባልን ስሜታችንን አንገማመትም:: ይነግረኛል አውቃለሁ። እነግረዋለሁ ያውቃል።
“ቤተሰቦችህጋ ትደውላለህ?” አልኩት።
“አላውቅም!” አለኝ ከቤተሰቡ ጋር ለረዥም ዓመታት ተገናኝቶም ደውሎም አያውቅም።
ማውራት የማይፈልገው አጀንዳ ነው። እሱ ጴንጤ ከሆነ በኋላ ምንም አይነት መጠያየቅ ተጠያይቀው አያውቁም። ትዳራችን ላይ የሚያመጣው መዘዝ አለ ብዬ አስቤውም ስለማላውቅ ትኩረት ሰጥቼው የማውቀው ነገር አልነበረም።
ከዚህ ክስተት በኋላ ከዋነኛው ባሌጋ የምናነባቸው መፅሃፍት ውስጥ እንዳሉት ፍቅረኛሞች የሚያስቀና ትዳራችንን ቀጠልን። መፅሃፍቶቹ ውስጥ ያሉ ባለትዳሮችም ሆነ በገሃዱ አለም ያሉ ባለትዳሮች ሳይነግሩሽ የሚዘሏቸው ጥቃቅን የሚመስሉ ከባባድ ነገሮች አሉ። ለምሳሌ ምስር ወጥ ለመስራት ከወጡ ሙሉ ሂደት ምስሩን መልቀም እንደሚያደክም አይነግሩሽም ……. እርጉዝ ሆነሽ እንጣዬ ስታደርጊ ልጄን እየነካው ይሆን? የሚለው ሀሳብ ከስሜት እንደሚያወጣ አይነግሩሽም። (ምነው እማ? ሲለኝ በመሃል ልጁን ትነካው እንደሆነ ሃሳብ መጥቶልኝ ስለው አቋርጠን ለሰዓታት በሳቅ መዛላችንስ?)
የሰርጋችን ቀን ተወሰነ። ሽማግሌ ተላከ። ሆዴ እየገፋ ሲመጣ ደም ማነሴ እየጨመረ መጣ። ስለሚያዞረኝ ድንገት እንዳልወድቅ እርሱ እንደህፃን እጄን ይዞኝ ካልሆነ በቀር ከቤት አልወጣም። የሆነ ቀን እንጀራ የሚጋግሩልኝ ሴትዮ ‘ምጣዱ ተሰበረ’ ሲሉኝ። አብሪያቸው ምጣድ ላጋዛ ገበያ ሄድኩ።(ይሄንንም አይነግሩሽም በነገርሽ ላይ)
ገበያው መሃል ጎንበስ ብዬ ቀና ስል አዙሮኝ ወደቅኩ። እኔ እቤት ሳልደርስ ወሬው ባሌጋ ደርሷል። ሲመጣ እጅ እግሩ እየተንቀጠቀጠ ደባብሶ ደህና መሆኔን ካረጋገጠ በኋላ ….. ልቡ በአፉ ልትወጣ እስኪደርስ ደንግጧል። ከዛ ያልገባኝ የድንጋጤው ብዛት ወደ ቁጣ ተቀየረ።
“አትውጪ አላልኩሽም? አይቀርም? ለምን ሰው የሚልሽን አትሰሚም? የሆነ ነገር ሆነሽ ቢሆንስ? ” (ያ ደባሉ ባሌ መጣ) ረስቼው ነበር እና አላስተዋልኩትም።
“በቃ ምንም አልሆንኩምኮ ! በጣም አካበድክ” ከተኛሁበት ብድግ አልኩ እሱ በሚናገርበት ድምፅ ጮክ ብዬ (ምላሴ ቢያርፍስ ?)
አንዴ በጥፊ ሲያልሰኝ እኔ ከሲኖትራክ ልውደቅ ሲኖትራኩ በኔ ላይ ይሂድ አላውቀውም! ብቻ ስሜቱ እንደዛ ነው። የሰው ጥፊማ እንዲህ ጭው አይልም።
አመንኩ። ይሄ የአንድ ቀን ስህተት አይደለም። ባሌ ሁለት ነው። እሺ ምን የሚሉት ነው? ፍቅር ነው ጥላቻ? በምነኛው ዘርፍ ልቀበለው? ነፍሱ እስክትወጣ ስለሚያፈቅረኝ የሆነ ነገር ሆነሽብኝ ቢሆን ኖሮስ ብሎ ተናዶ እርጉዝ ሚስቱን እሱ በነፃ በአንድ ሲኖትራካዊ ጥፊ የሆነ ቦታ ደርሶ መልስ ትኬት የሚያስቆርጠኝን ባሌን በምን ዘርፍ ልመዝግበው? ለሁለት ባል እያወቅኩት ልሞሸር?
(እዚህ ክፍል ድረስ ከዘለቃችሁ ይሄን ልንገራችሁ። የሆነችዋ ሴት በዚህ መንገድ አልፋለች ወይም እያለፈች ነው። ምናልባት ለሆነችዋ ሴት ብርታት ሊሆን ይችላልና ይህ የእኔ የሜሪ እውነተኛ ህይወት ነው። ብታምኑም ባታምኑም ስፅፈው ከ17 ዓመት በኋላ ከእንባዬ ጋር ነው። የስራችሁን ይስጣችሁ በቀን ሁለቴ ታስቸክሉኛላችሁኣ?)

One Comment

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...