Tidarfelagi.com

‹ሀገር ማለት ሰው ነው›፤ እስኪ ሙት በለኝ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገርሙኝ ዘፈኖች አንዱ ‹ሀገር ማለት ሰው ነው› የሚለው ነው። እሥራኤላዊና ጂፕሲ ይህንን ቢሰሙ ምን ይሉ ይሆን? እላለሁ። አይሁድ በመላው ዓለም ለ1900 ዓመታት ያህል ተበታትነው ሲኖሩ በየአካባቢው ሰው ነበራቸው፤ያውም እንደ ብረት የጠነከረ ማኅበረሰብ፤ ሀገር ግን አልነበራቸውም። ሀገር ማለት ሰው ከሆነ አይሁድ ሀገር ፍለጋ ከሺ ዓመታት በላይ መኳተን አልነበረባቸውም። በአውሮፓ የሚኖሩት ጂፕሲዎች የታወቀ ማኅበረሰብ አላቸው። ነገር ግን ሀገር የላቸውም። ሀገር ማለት ሰው ቢሆን ኖሮ ጂፕሲ የሚባል ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ጂፕሲ የሚባል ሀገርም ይኖር ነበር። ግን የለም።

በአሜሪካ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን አሉ። ‹በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን› የምትባል ሀገር ግን የለቺም። 1.3 ሚሊዮን የሚደረሱ ግሪኮች በአሜሪካ ይኖራሉ። ‹የአሜሪካ ግሪኮች› የምትባል ሀገር ግን የለችም። ‹ግሪክ ሲሠራ አሜሪካ ይኖራል፣ ሲያረጅ ግሪክ ይጦራል› የተባለው ሀገር ሰው ብቻ ስላልሆነ ነው።

ሰዎች ተሰብስበው ሀገር ሊመሠርቱ አይችሉም። በየሀገሩ የተሰበሰቡ ማኅበረሰቦች ‹ኮሙኒቲ› ይባላሉ እንጂ ሀገር አይባሉም። ሀገር ሀገር ለመሆንና ለመባል ከሰው በተጨማሪ የምትፈልገው ብዙ ነገር አላትና። ሀገርን ሀገር ለማስባል መሬትም ያስፈልጋል፤ መሬት ሳይኖርህ ሰው ስለሰበሰብክ ብቻ ሀገር ልትሆን አትችልም። ያውም የእኔ የምትለው፣ የምትሞትለትና የምትለፋለት ታሪካዊ መሬት ያስፈልግሃል። አይሁድ በ1930 አካባቢ በኡጋንዳ ኡዋሲን ጊሹ (Uasin Gishu County) በተባለ ቦታ እንዲሠፍሩና ሀገር እንዲኖራቸው ታስቦ ነበር። እንደ ቴዎዶር ኸርዝል ያሉ ታላላቅ የጽዮናዊነት መሪዎችም ለጊዜውም ቢሆን ተስማምተውበት ነበር። ብዙኀኑ አይሁድ ግን ‹ሀገር ማለት የሆነ መሬት አይደለም። ታሪካዊ መሬት ነው› ብለው ተቃወሙት፤ ሀገር ማለት የሆነ መሬት ብቻ ቢሆን ለአይሁድ ከዛሬዋ እሥራኤል ይልቅ በአየር ንብረትና በተፈጥሮ ማዕድን፣ ብሎም በአቀማመጥ ኡጋንዳ ትሻላቸው ነበር።

ባድሜ ለምትባል ከጦርነቱ በፊት ብዙው ሕዝብ ሰምቷት ለማያውቅ መሬት የተደረገውን ጦርነት የረሳ ሰው ነው ‹ሀገር ማለት ሰው ነው› የሚል። ሀገር ማለት ሰው ከሆነ ለባድሜ የተደረገው ጦርነት ለማን የተደረገ ነው ሊባል ነው። በሄግ ፍርድ ቤት የነበረው ክርክርስ የመሬት ክርክር እንጂ የሰው ክርክር ነበር እንዴ? ሀገር ማለት ሰው ቢሆን ኖሮ ሰው ስለ ሀገሩ ሲያነሣ ወንዙን፣ ተራራውን፣ ሸለቆውን፣ ሜዳውን፣ ጫካውን እያነሣ ለምን ይዘፍን ነበር ።

‹ያገሬ ተራራ ወንዛ ወንዙ ለምለም
እማማ ኢትዮጵያ ኑሪ ለዘላለም› ለምን ይል ነበረ።
ሀገር ማለት ሰው ከሆነ ይሄ የኔ ክልል፣ ጎጥና መንደር ነው የሚለው ክርክር ከየት ይመጣ ነበር? ሀገር ማለት ሰው ከሆነ የተለየና የታወቀ የሀገር ድንበርና ካርታ ለምን ያስፈልግ ነበረ? ሰውማ የትም ነው የሚኖረው። ካርታ አያሻውም። ሀገር ማለት ሰው ከሆነ ለምን የአብዛኞቹ ሀገሮች ብሔራዊ መዝሙር ስለ መሬቱና ስለ ድንበሩ ያወራል? ሀገር ማለት ሰው ከሆነ ለሰው ፓስፖርትና ቪዛ ለምን ያስፈልገዋል? ሰው ያለበት ቦታ ሁሉ ሀገሬ ስለሆነ ለምን እንደፈለግኩ ወጥቼ አልገባም? አንድ ሰው ወደ አንድ ሀገር ገባ የሚባለው ወደ መሬቱ ሲገባ እንጂ የሀገሩን ሰው ሲያገኝ ነው እንዴ? ምናልባትም ከአንታርክቲካ በቀር ቪዛ መጠየቅ ያለበት ሀገር አልነበረም። እርሱ ሰው የለበትምና ‹ሀገር ማለት ሰው ነው› የሚለው አይመለከተውም። ሀገር ማለት ሰው ከሆነ በሰማይ የሚሄድ አውሮፕላን ‹የአየር ክልሌን ጣሰ› ብሎ መሟገት ምን የሚሉት ሞኝነት ነው? ሰውን አልጣሰ፣ የጣሰው አየር ነው።

ደግሞም አገር ማለት መሬት ብቻ አይደለም። ያማ ቢሆን ኖሮ አንታርክቲካ ሀገር ይሆን ነበር። ያማ ቢሆን ኖሮ በዓለም ላይ የሚገኙ ወደ ሃምሳ የሚጠጉ ሰው አልባ ደሴቶች(nonecumene)‹ሀገር› ተብለው በተባበሩት መንግሥታት ይመዘገቡ ነበር። ሀገር ማለት መሬት ቢሆን ኖሮ መሬት ያለው ሁሉ ሀገር ይኖረው ነበር። የአሜሪካ ሕንዶች፣ የአውስትራልያ አቦርጅኖች፣ ከጥንት ጀምሮ የሚኖሩበት መሬት አላቸው። የራሳቸው የሆነ ሀገር ግን የላቸውም። ደቡብ ሱዳናውያን የራሳቸው የሆነ የሚኖሩበት መሬት ነበራቸው፤ ሀገር ለመሆን ግን መዋጋት ነበረባቸው። ደቡብ ሱዳኖችን ያን ሁሉ ዘመን ያዋጋቸው የመሬት ጥያቄ ሳይሆን የሀገርነት ጥያቄ ነው። የራሳቸውን ፖለቲካዊ መሬት አግኝተው እንኳን ሀገር ለመሆን ገና እየተሠሩ ነው። ፍልስጤማውያን ይብዛም ይነስ የሚኖሩበት መሬት አላቸው። አገር ግን የላቸውም።

አገር ከዚህ ሁሉ በላይ ነው። ሰው፣ ሰው የኖረበትና ታሪክ የሠራበት መሬት፣ ማኅበረሰብ ከማኅበረሰብ፣ ሰው ከሰው፣ ሰው ከማኅበረሰብ፣ ሰው ከመሬት፣ ሰው ከአራዊት፣ ሰው ከተፈጥሮ፣ ሰው ከወራሪ ጋር የነበረው ትግል፣ ውጊያና ወዳጅነት፤ የተረተው ተረት፣ ያወጋው ወግ፣ የፈጠረው አፈ ታሪክ፣ ያከማቸው ትዝታ፣ ሰው ለመሬቱ፣ ለወገኑና ለእምነቱ የከፈለው መሥዋዕትነት፤ የዘፈነው ዘፈን፣ ያቅራራው ቀረርቶ፣ የፎከረው ፉከራ፤ ያገኘው ድልና የተሸከመው ሽንፈት፤ ያደረሰው በደልና የደረሰበት በደል ይሄ ሁሉ ነው ሀገር።

መገለጫው ቅርስ፣ መዋሐጃው ባህል፣ መታያው ልብስና መዋቢያው ጌጣጌጥ፣ መገናኛው ቋንቋ፣ መዝናኛው ጭፈራ፤ ማስተማሪያው ተረት፣ መክበሪያው ዓመት ባል፣ መጠበቢያው ምግብ፣ መቆዘሚያው እንጉርጉሮ፣ መተከዣው ልቅሶ፣ መተኪያው ልደት፣ ማሳረጊያው ቀብር፤ መገምገሚያው ምግባር፣ ማነወሪያው ነውር፤ መኩሪያ ጀግንነቱ፣ ማፈሪያ ገመናው፤ መደበቂያ ቤቱ፣ መመረሪያ ጫካው፤ ይሄ ሁሉ ነው ሀገር። ታሽቶ ተገርኝቶ ያመጣው አንድነት፣ ተጣልቶ ተባልቶ ያመጣው ልዩነት፣ እንደ ዘሐ ዘጊ የተጠላለፈው፣ እንደ እግር ሠንሠለት የተቆላለፈው፣ ሲፈተል፣ ሲገመድ፤ ሲባዘት፣ ሲዳውር፤ ሲከካ፣ ሲሰለቅ፤ ሲጣላ፣ ሲታረቅ፤ ሲያውቅና ሲማይም፤ ሲሠለጥንና ሲደኸይ፤ ሲሰፋና ሲጠብ፤ የኖረውና የኖረበት፣ የኖረለትም ነው ሀገር።
ሀገር ትዝታ ነው። የትም ቦታ ስትሄድ ጠምዶ የሚያመጣህ። ምንም ሥጋ ብትቆርጥ ከብቱ ትዝ ይልሃል፤ ምንም ቢች ዳር ብትዝናና ወንዙ ትዝ ይልሃል፤ ምን በሽቱ ብትታጠን አፈሩ ይሸትሃል፤ ምን በሥጋጃ ላይ ብትሄድ ጉዝጓዙ ይመጣብሃል። በኮምፒውተር እየሠራህ ያቦካኸው ጭቃ ይናፍቅሃል፤ በጄት እየበረርክ አህያና በቅሎው ያምርሃል፤ ማንሐተን ተቀምጠህ ሰባተኛ፣ ሎንደን ተቀምጠህ ቂርቆስ፣ ኖርዌይ ሆነህ ጅግጅጋ፣ ካናዳ ሆነህ ሐረር ይወዘውዝሃል። ሀገር ማለት ትዝታ ነው።

ሀገር ማለት ከምትገልጠው ብታስበው፣ ከምትኖርበት ብትሞትበት፤ ከምትስቅለት ብታለቅስለት የምትመርጥለት ነገር ነው፤ ሀገር ማለት ትተህው ብትሄድ ትቶህ የማይሄድ፣ በራቅከው ቁጥር ልብህ ውስጥ የሚቀር፣ ባወቅከው ቁጥር የምትንገበገብለት፤ በተረዳኸው ቁጥር የምትሳሳለት፣ አንተን እርሱ ውስጥ እንደምታገኘው ሁሉ እርሱንም አንተ ውስጥ የምታገኘው፤ የተሠራህበት ውሑድ፤ የተቀረጽክበት ማንነት ነው ሀገር።
ሀገር ማለት ሰው ብቻ ቢሆን ኖሮ ዘመድ የሌለው ሰው ወደ ሀገሩ ለመምጣት ባልናፈቀ ነበር። ሀገር ማለት ሰው ብቻ ቢሆን ኖሮ ዘመዶቹ ሁሉ ከእርሱ ጋር ውጭ የሚኖሩለት ሰው ‹ሀገሬን ሀገሬን› እያለ መከራ ባላየ ነበር። ሀገር ማለት ሰው ብቻ ቢሆን ኖሮ ሰዎች በየዘመናቱ የበደሉት ሰው ሀገሬ በደለችኝ ባለ ነበር። ሀገር ማለት ሰው ብቻ ቢሆን ኖሮ ሰው ስለ ሀገሩ ሲያስብ ተራራውና ወንዙ፣ አዕዋፉና አራዊቱ፣ ማሳውና ቀየው ለምን ትዝ ይለው ነበር። በሀገር ማለት ሰው ብቻ ቢሆን ኖሮ ያሸነፈ አትሌት፣ ድል ያደረገ ኳስ ተጨዋች ባንዴራው ሲሰቀል ለምን ያለቅስ ነበር?
‹አዙረሀ አዙረህ ሀገሬ መልሰኝ
በሹም ታዘዘ አፈር አታልብሰኝ› ብሎ ለምን ያንጎራጉር ነበር። ዐጽሙ በአፈሩ እንዲያርፍ ለምን ይናዘዝ ነበር። ለምን ሙሾውን፣ የሠርግ ዘፈኑን፣ ወጉን ማዕረጉን ይፈልገው ነበር።

ሀገር በአርምሞ እንጂ በንግግር፣ በተግባር እንጂ በዝርዝር ሊናገሩለት የማይቻል ነገር ነው። ውጥንቅጥ ሰበዞች የሰፉት ሞሰብ፣ዓይነተ ብዙ ድርና ማጎች የሸመኑት ጋቢ፣ ልዩ ልዩ ቅመሞች የሠሩት ወጥ፣ ብዙ ገባሮች የፈጠሩት ዓባይ፣ ብዙ ትውልዶች የከመሩት ተራራ፣ ከአራቱ አቅጣጫ ተሰብስቦ በአንድ ወፍጮ የተፈጨ እህል፣ ከየአበባው ተቀስሞ በአንድ ቀፎ የተሠራ ማር፣ ከየእህሉ ወጥቶ በአንድ ማድጋ የተጠመቀ ጠላ፣ ከየ እንጨቱ ተለቅሞ በአንድ ጽንሐ የታጠነ ዕጣን ነው ሀገር።
ሀገር ማለት ሰው ነው? እስኪ ሙት በለኝ

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...