Tidarfelagi.com

ሀገርኛ በሽታ ይዞ፣ የባህር ማዶ መድሃኒት የመፈለግ ክፉ አባዜ

አንዳንድ ሰዎች አሉ፤ያልተማሩ የምናላቸው። ሲያማቸው ጎረቤታቸው ጋር ሄደው «ባለፈው እንዲህ እንደኔ ሲያምህ ሀኪም የሰጠህ መድሃኒት የቷ ነበረች? » ብለው ተቀብለው ያለምንም ምርመራ የሚውጡ፤ እቺን ሀገር የመሰሉ!!

የውጭውን ሁሉ እያመጣን እላያችን ላይ ማራገፋችን ለዓመታት የሚከተለን ችግር ነው። እየተከተለ ይኮረኩማናል። አንሰማም። አንነቃም።
የዛ ትውልድ አባላት ሃያ ፐርሰንት የማይሞላ ላብ አደር ባላበት የላብ አደሩን አንባገነንነት የሚፈቅደውን ስርዓት ናፈቁ፣ዘፈኑ። ደርግ መጥቶ ቀጠለው።ገደለለት። ምን ተገኘ? ምንም!

ቴዎድሮስ አንድ የሚደነቅ ነገሩ(አካሄዱ አጉል ቢሆንም) የውጭዎቹን ስልጣኔ የደረሰበትን የመሳሪያ ጥበብ እዚህ ልስራ ማለቱ ነበር። ይሄን ፍቅረማርቆስ ደስታ በጥሩ መልኩ ባንድ መፅሐፉ ጠቅሶታል።
ሌሎች ነገስታት «ላኩልኝ» ባዮች ነበሩ።ማዘመን ላይ የተሰራው ስራ አብዛኛው እጅ የመቀበል ነው። እውቀቱን አይደለም፣ ያለቀ የደቀቀውን እየጠቀሱ እጅ መዘርጋት። ኢትዮጵያ እጆቿን ትዘረጋለችን እያስታወሱ…

የውጭውን አምጥቶ ራስ ላይ እየናዱ ማደግ፣መለወጥ ይችላል የሚል አባዜ ለተከታታይ ትውልድ አልፈታንም።በግሌ፣ አንድ አገር ሊያድግ የሚያችለው በራሱ አካሄድ እና ህዝባዊ ስነልቦና በቀረፀው ስርዓት እንደሆነ አምናለሁ።

አፄ ሚኒሊክ፣ ሚኒስትሮቻቸውን ሲሾሙ ፈረንጆቹን ለመምሰልና «እኛም ሾመናል፣እናንተን መስለናል»በማለት «ዘመናዊ አስተዳደር» ጀመርን ከማለት ባለፈ፣ መሰረታዊ ለውጥን ተከትሎ አልነበረም።ስርዓት አልተከለም።
ሃይላስላሴ ህገመንግስቱን ሲቀርፁ፣ ለሊግ ኦፍ ኔሽን አባልነታቸው አንድ ማሟያ እንጂ ከልብ የተበረከት ፈንክሽናል ህግ አልነበረም። የቅበላ ነገር እንዲህ ነው።
ሌላውንም ፈፅሞ አለመምሰል፣ ከራስም ጋር መነጠል ነው ውጤቱ።

ደርግ መጣ። ለሕዝቡ ግራ፣ለራሱም በቅጡ ያልገባውን ርዕዮተ ዓለም ሲያንበለብል ከረመ። አጥናፉ አባተ «ኸረ ይሄ ሶሻሊዝም ብለን ያመጣነው ስርዓት ለሕዝባችን የሚሆንም አይደል» አለ። የፈጠረው አብዮት በላው (መንግስቱ ሃይለማርያም «በትግላችን መፅሐፉ በሹፈት እንዳለው!) በሌላ ቅንፍ ( አብዮቱ እራሱ መንግስቱ ሳይሆን አይቀርም)

የዛሬዋም ከትምህርት ስርኣቱ እስከ ፀረ ሽብር አዋጁ ከነጮቹ መቅዳቷን ሳታፍር ትጮሃለች። «ቃል በቃል ከአሜሪካ ነው የቀዳነው» ተብሎ ይቀደዳል።ማፈር ኋላ ኪስ ገብታ ቁጭ ብለውባታል።
ካሪኩለም ነሽ፣ ቢፒአር፣ ካይዘን ነሽ ጂኒ ጃንካ ይመጣና ይራገፋል። ያንድ ሰሞን ሙቀት ይሆናል። ስለ ስራ ከጉራጌ ሕዝብ ያልተማረ ሀገር፣ አቁማደውን አንከርፍፎ ጃፖን ወርዶ ካይዘን የሚባል ነገር አዝሎ ስለመጣ፣ ጉሮሮውንም ስላደረቀ ለውጥ ያመጣ ይመስለዋል። በተጨባጭ ምንም የለም። መደናቆር።

ሀገርኛ በሽታ ይዞ፣ የባህር ማዶ መድሃኒት የመፈለግ ክፉ አባዜ።
«ባለፈው ሰሞን እንዲህ እንደኔ ሲያማችሁ የዋጣችሁት መድሃኒት የቱ ነበር? » ያለምርመራ ተቀብሎ ዋጥ!! ሌላ በሽታ!

ትምህርቱን እዩት። ዮናስ አድማሱ ባለፈው ሳምንት በሸገር የተናገሩት ጥሩ ምሳሌ ነው።ስለ ዓለም ታሪክ ስንማር ስለሃገራችን ይሄ ነው የሚባልም አንማርም ነበር ጭብጡ።
ናሽናሊስት አይደለሁም። ከሌሎች ሀገር ተሞክሮ የመውሰድ አስፈላጊነትም ሳይገባኝ ቀርቶ አይደለም። ዝም ብለው እያመጡ ማራገፍ ግን እንደ አዲስ አበባ ከመቆሸሽ ውጪ ፋይዳ ያለው አይመስለኝም።
የጃፓን ስልጣኔ ማዋራስ ነው ብለውናል።ወንፊት ሳይዙ በእጅ በአፍ በመቀበል አይደለም።

ዛሬ ይሄ ይበጀናል፣ ይሄ አይበጀንም የለም። ከኛ ይሄዳል አይሄድም የለም። ዝም ብሎ ማግበስበስ ብቻ። ከዛ «ቃል በቃል» እያሉ ሳያፍሩ መፎለል ይከተላል።
እደግመዋለሁ፣ ዝም ብለው እያመጡ ማራገፍ ግን እንደ አዲስ አበባ ከመቆሸሽ ውጪ ፋይዳ ያለው አይመስለኝም።
ሃሃሃሃሃ አዲስ አበባን ለማፅዳት እንኳን ተሞክሮ ለመውሰድ ኪጋሊ ነው አሉ የሄድነው፣ ባህርዳርን አላየንም።
መረገም ነው።
ስላዳመጣችሁኝ ገለቶማ
ጣናን ኬኙማ (ድሮ የማን ነበር? ወስደው የመለሱልንን መንግስታት እናመሰግናለን 🙂 )

የራስ ናቸው፡፡ የማንንም ሃሳብ ለመፃፍ አልተከፈተም! የሚያስማሙንን ሃሳቦች እዚህ ካገኛችሁ እሰየው፡፡ ለመስማማት አንፅፍም፣ ለመፃፍ አንስማማም፡፡ ወዘተ

One Comment

 • Melaku Endashaw commented on October 15, 2017 Reply

  ሚኒሊክ የዘመናይት ኢትዮጵያ ጀማሪ እንደመሆኑ የተወሰኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ወደሃገር ከማስገባት ባለፈ የተደራጀ ስርዓት የመኮረጅ እድል አልነበረውም። ያኔ በነበረው የመገናኛና የመጓጓዣ ዘዴዎች ውስንነት አለም ብዙም አይተዋወቅም ነበር። እንኳ ጠቅላላ ሲስተምን ቀርቶ አንድን እቃ ለማስመጣት ከወራት እስከ አመታት ይፈጅ እንደነበረ አይረሳም። በኔ እምነት ምኒልክን ለመውቀስ የሚያበቃ ምክንያት የለንም።

  2) አፄ ሃይለስላሴ ሲስተሙን ማዘመኑ ላይ ጥሩ አጀማመር ቢያሳዩም ከሃገር እድገት ይልቅ ስለግል ክብራቸው ሲጨነቁ ሃገሪቷን ትልቅ ዋጋ አስከፍለዋታል። ከሁሉም መንግስታቶቻችን በቁጭት የሚያንገበግብ ጊዜ ቢኖር የሳቸው የመሪነት ወቅት ነው። ግማሽ ምዕተ ዓመት ቀርጥፈው በልተዋል።

  3) መንግስቱ ከራሱ ውጭ የማንንም ሃሳብ የማይሰማና ጨካኝ ስርዓት ያሰፈነ ቢሆንም ለተከተለው ርዕዩተዓለም ልንወቅሰው አንችልም። እሱ ብቻ ሳይሆን በወቅቱ የነበሩት አብዛኞቹ የፖለቲካ ሃይሎች ሶሻሊዝም መለያቸው ነበር። ሶሻሊዝም በወቅቱ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለብዙ ሃገራት የኣብዮት ምክንያት ነበር። በነገራችን ላይ ይሄ ርዕዩተዓለም ነክቶት ያለኪሳራ ያስተረፈው ሃገር የለም። አሁንም ከኢሃዴግ ተቃዋሚዎች አካባቢ ሳይቀር የዚህ ስርዓት አፍቃሪዎች አሉ።

  4) ዌል እንግዲክ፡ ህወሃት/ኢሃዴግን እንደመንግስት ለመተቸት በጣም ያስቸግራል፡ ምክንያት ደግሞ አሁን ድረስ እንደወራሪ እንጂ እንደመንግስት አክት ስለማያደርጉ። በፊት በደርግ ላይ ሸፍተው ጫካ ገቡ፣ ደርግን ጥለው ከተማ ሲገቡ ደግሞ ህዝቡ ላይ ሸፈቱ። እነሱ አማፂ እንጂ መንግስት አይደሉም። ስለዚህ ስለሽፍቶች ማውራቱን ትቻለሁ።

  የተማረ ከሚባለው አካባቢ ተደጋግሞ ሲነገር የምንሰማው የፈረንጆቹን (ፍሬንቾችን) በቀጥታ ለመቅዳት ስለምንሞክር ነው ያልተሳካልን የሚል ነገር እኔ አልቀበለውም። እንደውም በሚገባ ስለማንኮርጅ ነው ችግራችን። በተለምዶ ፈረንጆች የምንላቸው አውሮፓውያንና አሜሪካ በተግባርና በልምድ የተፈተነ፣ በጽሁፍ ጭምር የተደገፈ እውቀት አላቸው። የትኛው አሰራር ወይም ዕውቀት ከየትኛው ሃገር እንደወጣ አይከራከሩበትም፤ ነገር ግን ጠቃሚ ሆኖ ያገኙትን ተኮራርጀው የደረሱበት ደርሰዋል። የኛ ችግር ስንኮርጅ አሰራሩን ትተን የመጨረሻ መልሱን ብቻ መሆኑ ነው። በሳይንሱ መሰረት አንድ ነገር ሲሰራ ተጠንቶ፣ ታቅዶ፣ ተነድፎ ተሞክሮ ነው። እንደሳይንሱ በእያንዳንዱ ሂደት ውስጥ ምንምን ነገሮች ከግንዛቤ መግባት እንዳለባቸው፣ ለያንዳንዱ ሁኔታ የትኛው ዘዴ ጥቅም ላይ መዋል እንዳለበት ዲቴይል ነገሮች ይቀመጣሉ። ሳይንሱን ከፈረንጆቹ እንዳለ ገልብጠን ቢሆን ኖሮ እነዚህንም ነገሮች አብሮ ማምጣት ይገባን ነበረ፤ ግን አይደለም። አኮራረጁን አላወቅንበትም።

  እንደኔ እይታ የሃገሪቱ መንግስታት ዋና ችግር የኣሰራር አይደለም፤ የሰሪ መጥፋት ነው። ስራውን የሚሰራ መንግስት ኖሮን አያውቅም። ዋናውን ሃገርን የመገንባት ስራ ትተው ስልጣናቸውን ሲጠብቁ ነው የሚባትሉት። የነሱን ስራ ልምድና ዕውቀት ለሌላቸው አቤት ባዮች ትተው በወንበራቸው ላይ ያንቀላፋሉ። ወንበራቸው ካልተንገጫገጨ ለሰላምታ እንኳ አይነቁም።

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...