‹‹አላቅሱኝ››

ትላንት አባቴ ሞተ።

ካሁን በኋላ በለመድናት ሰአት የውጪ በራችንን በቁልፉ ‹‹ቃ›› አድርጎ ከፍቶ ላይገባ፣ ካሁን በኋላ ሳመሽ በረንዳ ላይ ጋቢውን ለብሶ እሳት ጎርሶ ጠብቆ ላይቆጣኝ፣ ካሁን በኋላ የአመት በአል ድፎ እየሳቀ ላይቆርስ፣ ካሁን በኋላ ልጄን፣ የልጅ ልጁን አቅፎ ላይስም… ሞተ።
አባቴ ሞተ።
ክትት አለ። አባቴ አፈር ሊሆን ሞቶ በሳጥን መጣ።

ለቀስተኞች ‹‹ላያስችል አይሰጥምና ቻይው›› ይሉኛል። ሃዘኑን ቢሰጠኝም መቻያውን እንዳቀበለኝ በምን አወቁ?
‹‹እኛም እንከተለዋለን፣ ሞት እኮ አይቀርም..ሁሉም ተራውን ጠባቂ ነው ›› ይሉኛል። የእኛ በተራችን እሱን መከተል የሱን የዛሬ ሞት ያቀልለዋል የሚለው መደምደሚያ ላይ እንዴት ብለው ደረሱበት?

ቀዳዳዎች።
ወሬኞች።

ከሁሉ በላይ ግን የሚብሱት ‹‹ ሁሉ ነገር ለበጎ ነው። ይሄም ለበጎ ነው›› ባዮቹ ናቸው።

ደደቦች።

ይሄን እንዳሉ እዛው ወደ አመድነት ቢቀየሩ እመኛለሁ።
የጨው አምድ ቢሆኑ እፈልጋለሁ።
ሲኖ ትራክ እየከነፈ መጥቶ ቢደፈጥጣቸው፣ ዳምጠው መኪና መጥቶ ቢዳምጣቸው፣ የመቶ አመት ዛፍ ግ-ን-ድ-ስ ብሎባቸው ክልትው ቢሉ ደስ ይለኛል።

ኤሌክትሪክ ቢያደርቃቸው፣ ትንታ በአንድ ጊዜ ዝም-ጭጭ ቢያደርጋቸው እርክት እላለሁ።

እስቲ አሁን በምን ስሌት ነው የኔ ደግ አባት ከእኛ ቀብቃባ የድሮ አለቃው አቶ ክንፉ በፊት መሞቱ ለበጎ የሚሆነው?
እኮ በምን ሂሳብ ነው የኔ ቅን አሳቢ አባት ከዚያች መሰሪ ጎረቤታችን ንግስት በፊት አፈር መሆኑ ለበጎ ነው የሚያሰኘው?
ምን ሲሆን ነው የኔ አለም- የኔ ሁለንተና- አባቴ… ከነዚህ ወሬኞች በፊት ድንጋይ መሸከሙ ለጥሩ የሚሆነው?

በጎነቱስ ለማን ነው?

አፅናንተው ሞተዋል። እርጉሞች።

ሰው እንደኔ ቀኑ ሲጨልምበት፣
የአለም ውሃ ልክ ሲዛባበት፣ ነገር ሁሉ ሲዛነፍበት ‹‹እንዴት ያለው ክፉ ነገር አገኘህ…እንዴት ያለው መጥፎ እድል አጋጠመሽ!›› ብሎ በማፅናናት ፈንታ፣ ክፉን ደግ፣ ጨለማውን ብርሃን፣ መራራውን ጣፋጭ፣ ሜዳውን ገደል ለማድረግ የሚሞክሩ ሰዎች ይፈትኑኛል።
በንዴት አግመው እጄን ያንቀጠቅጡታል።
ፀጉሬን ያቆሙታል።
ጥርሴን ያፋጩታል።

ሁሉም ነገር እኮ በጎ ጎን የለውም። ክፉ ነገር ሁሉ እኮ በጎ ተከታይ የለውም።
አንዳንዱ ጨለማ እኮ አይነጋም።

እንደኔ አባት ሞት ያለው ነገር የአለም ጨካኝነት ውጤት ነው።

ክፉ ብቻ ነው።
አስጠሊታ ብቻ ነው።
ጨካኝ ብቻ ነው።
መራር ብቻ ነው።
ገደል ብቻ ነው።

በቃ።

ሁለት ወልዳ አንዱ የሞተባት እናትን ‹‹አይዞሽ ቢያንስ አንዱ ልጅሽ አለልሽ›› ማለት ማፅናናት ነው?
ሁለት እንቁላል ኖሯት አንዱ አልተሰበረባትም እኮ!
አንድ አይነት አይደሉም። ልጆች ናቸው። ሰዎች ናቸው። መልካቸው ይለያያል። ሳቃቸው ይለያያል። ስማቸው ይለያያል። ህልማቸው ይለያያል። ሲወለዱ እንኳን ምጣቸው ይለያያል።

አንድ እግሩን በአደጋ የተቀማ ወጠምሻን፣ ‹‹ ቢያንስ ሌላኛው እግርህ ተርፏል››
አንድ አይኗ የጠፋን ሴት፣ ‹‹ ቢያንስ አንዱ ቀርቶልሻል››
‹‹ትዳሬ ፈረሰ›› ብሎ የሚተክዝ ጎልማሳን፣ ‹‹ሁሉም ነገር ለበጎ ነው ቢያንስ የትዳርን ሕይወት አጣጥመኸዋል››
‹‹ልጅ አስወረደኝ›› የምትል ሴትን ፣‹‹ ቢያንስ አርግዘሽ ነበር። እንግዲህ ሁሉም ነገር ለበጎ ነው ላያድግ ይችል ነበር›› ማለት ማፅናናት ነው?

እንደኔ አባት ሞት ያለው ነገር የአለም ጨካኝነት ውጤት ነው።

ክፉ ብቻ ነው።
አስጠሊታ ብቻ ነው።
ጨካኝ ብቻ ነው።
መራር ብቻ ነው።
ገደል ብቻ ነው።

በቃ።

ስለዚህ አነዚህ ቀፈፊዎች ፤

በጥቁር ደመናዬ ላይ ቀስተ ደመና ለመሳል ከሚሞክሩ፣
በጥቁር ሰማዬ ላይ የብድር ፀሃይ ከሚያንጠለጥሉ፣
በጨለማ መንገዴ ላይ አይን የሚያውክ ፓውዛ ከሚተክሉ፣
የለበስኩት ማቅ ጨርቅ ላይ ደማቅ ጥለት ከሚሸምኑ፣

ይሄንን አንጀት በጣሽ ሃዘን በዙሪያ ጥምጥም ለበጎ ከሚያደርጉ፣

‹‹እህቴን! እንዴት ያለው ክፉ ነገር ደረሰብሽ…!እንዴት ያለው መአት መጣብሽ….አይዞሽ›› እያሉ ቢያቅፉኝ፣ እያለቀሱ ቢያላቅሱኝ፣ ለሃዘኔ የሚመጥነውን እውቅና ቢሰጡልኝ….

…ምንኛ ባፅናኑኝ።

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

One Comment

  • Anonymous commented on April 28, 2017 Reply

    hiwot emishaw betam enwodishalen enadenkishalen enakebrishalenm…edime tena yistilin

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...