ራሴው ማበዴ ነው

“ተሳፋሪዎቻችን ይህ የበረራ ቁጥር 206 ነው… … ” ጭንቅላቷ እየሸወዳት እንደሆነ የማውቀው እንዲህ ማለት ስትጀምር ነው። በግልቡ እብደቷ እየጀመራት ነው ማለት ነው። እናቴ ናት!!

ይሄን ሀረግ ማለት ከጀመረች ትርጉሙ የዛሬ 20 ዓመት ወደ ኋላ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሆስተስ የነበረችበት ዘመን ላይ ናት… … ማርጀቷን አታውቅም፣ እኔንም አታውቀኝም ፣ ባሏ እሷን ትቶ ጓደኛዋን እንዳገባ አታውቅም ፣ ንብረቷን እንደተቀማች አታውቅም ፣ ጡቶቿ እንደተቆረጡ አታስታውስም ………… አንዳንዴ ራሷንም አታውቅም ~ ሰው ካላያት ራሷን ትጎዳለች። እብደቷ ሲነሳባት መከራዬ ናት። ምሬቴ ናት። ስቃዬ ናት። …… ጥለሻት ጥፊ ጥፊ ይለኛል። ጭንቅላቴን በቅውሰቷ ትዋጀዋለች። ብገላገላት የምታስመኘኝ መንቻካ አሮጊት ትሆናለች። መድሃኒቷን አትውጥልኝም፣ እንድነካት አትፈቅድልኝም ፣ አምናኝ እንቅልፏን አትተኛም…… ከየት የምታመጣው እንደሆነ የማይገባኝ ጉልበት አላት…… ታጠፋበታለች። እንደእኔ የምትጠላውና የምትፈራው አይኖራትም።

“የማላውቅሽ መስሎሽ? ቅናታም መርዘኛ! …… መድሃኒቱን በምግብ ለውሰሽ ልታበይኝ? አንድዬን ልትወስጂብኝ? እኔ አይናለም በህይወት ሳለሁ ቤቴ ሊፈርስ?” ትለኛለች ያገኘችውን እቃ እየወረወረችብኝ። አንድዬ የምትለው አባቴን ነው። የድሮ ባሏን።

“ማነሽ ደግሞ አንቺ? ወደ ቤቴ ውሰዱኝ… …… ኡኡኡኡኡ… … መድሃኒት ሊያበሉኝ ነው።……”

ዶክተሯ መጥቶ መርፌዋን እስኪወጋት በሷ እብደት እኔ አብዳለሁ። ስትረጋጋልኝ እብዷ እናቴን ከጠባቂ ጋር እቤት አስቀምጬ እወጣለሁ። …… ያበደች እናት እንደሌላት፣ አንዲት የኑሮ ሰበዝ እንዳልጎደለባት ፣ እንደደላት ሴት ሁኜ…… አዘውትሬ እንደምለብሰው ሙሉ ልብሴን አጊጬ ወደ ስራዬ እሄዳለሁ።

“ ኪዳነ ምህረት ምን በደልኩሽ? ምነው ጌታዬ ስቃዬን ቆለልክብኝ? ምናለ ብትገላግለኝ?” ስትል ደግሞ ትርጉሙ ወደ አሁን ተመልሳለች ማለት ነው። ያሳለፈችውን ስቃይ እያስታወሰች መታመም ጀምራለች ማለት ነው። እብደቷ ሲተዋት ታስለቅሰኛለች። ሆዴ ኩርምትምት ይልላታል። እንዳሰቃየችኝ ታውቀዋለች። ላበደችባቸው ቀናት እንግልቴ ስትከፍለኝ ጡት የለሽ ደረቷ ላይ ለጥፋኝ ታባብለኛለች። ምን መስማት እንደምትፈልግ አውቃለሁ።

“እማ በህይወት እስካለሽ አልተውሽም። ምንም ብታደርጊ እችልሻለሁ።” እላታለሁ። አትመልስልኝም። ብቻ ጨምቃ አቅፋኝ ትንሰቀሰቃለች። የአዕምሮ ህሙማን ሆስፒታል መግባት ሞቷ ነው። ትለምነኛለች። ሁለቴ ገብታ ታውቃለች። ይብስባታል እንጂ አይሻላትም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሰውነቷም እየደከመ ህመሟም እያዛላት ነው። ትናንትና የሚሚን የሰርግ መጥሪያ ወረቀት ካየች ጀምሮ የበረራ ቁጥሯን መቁጠር ጀምራለች።

ሚሚ አባቴ ከሌላ ሚስቱ የወለዳት እህቴ ናት። ሰርጉን እኔም እናቴም እንደማንሄድ ያውቃሉ። ለምን እንደማይተውን አላውቅም። ባገኙት ሰበብና አጋጣሚ እኔና እናቴ ሰላም እንዳይሰማን ይታትራሉ። እማዬን ለማረጋጋት እማይኮነውን ሁሉ እየሆንኩ እንፈራገጣለሁ። በሚሚ ሰርግ ጉዳይ ግን ከእማዬ ይልቅ እንዳላብድ መጠበቅ ያለብኝ እኔ ነበርኩ። ምክንያቱም ሚሚ የምታገባው የልጅነት ፍቅረኛዬን ነው። የሰርግ ወረቀቱን ለእኔ አምጥተው የሰጡበት ምክንያትም እንደእናቴ እንዳብድላቸው ነው። ኡፍፍፍፍፍፍፍፍፍፍ……

እኔ በሙያዬ ጠበቃ ነኝ። ……… በአንድ ቅሌታም ከፍተኛ ባለስልጣን ኬዝ ሰበብ ስሜ በሀገሪቷ የናኘ ጠበቃ…… አስታወሳችሁትኣ? አያቱ ከሚያክሉ አሮጊቶች ጋር የሚወሰልተው ሰውዬ…… አዎን ለደፈራቸው የ70 ዓመት ምስኪን አሮጊት የቆምኩት እና ያስፈረድኩበት እኔ ነበርኩ። ያ መርገምት ካርቱሚስት በአንደኛው ሳምንታዊ ጋዜጣ ላይ ጥርስ የሌላት ድዳም እና ምላሷ ከፒያሳ እስከመገናኛ የሚደርስ አሮጊት አድርጎ የሳለኝ… … አዎን እኔ ነኝ። ……… አሁን ማን እንደሆንኩ አወቃችሁኣ?

“ቢሮሽ ሰው እየጠበቀሽ ነው።” አለችኝ ወይኗ ገና ከመግባቴ።

“ደህና አደርሽ ወይኗ።” ብዬ እየተጣደፍኩ ስገባ

“አባትሽ ነው። አባቷ ነኝ ነው ያለው። አባት እንዳለሽ አልጠረጠርኩም ነበር። ……” አለኝ ፍትህ።

“አባትሽ?” ተንደርድሬ ቢሮዬ ገባሁ። ደንግጦ ተነሳ። በዓይኔ ካየሁት እንኳን ሰባት ዓመት ሆኖኛል። ምናባቱ ሊሰራ ነው አሁን የሚፈልገኝ? ጭራሽ ቢሮዬ ድረስ?

ራሴው ማበዴ ነው (ክፍል ሁለት)

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...